ማንነት፣ ፍላጎት
እና ኃላፊነት።
ብርሃኑ ዳንኤል በማንነት፣ በፍላጎት እና በኃላፊነት መካከል ያለውን ግንኙነት ይመረምራል። ቀለም ቅብ የጥበብ ሥራው ማዕከል ሲሆን፣ በድሮዊንግ፣ በሕትመት ጥበብ፣ በቅይጥ ሚዲያ፣ በፎቶግራፍ፣ በአዲስ ሚዲያ እና በፐርፎርማንስ ጥበብም ይሠራል። በእነዚህ የጥበብ ዘርፎች አማካይነት፣ ማኅበረሰብ ስለ ራሳችን ያለንን ግንዛቤ እንዴት እንደሚቀርጽና የግል ፍላጎት በዙሪያችን ባሉ ሰዎችና አካባቢዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ይመለከታል።
በ1989 ዓ.ም. ተወልዶ በአዲስ አበባ ሾላ ሰፈር ያደገው ብርሃኑ፣ ገና በልጅነቱ ለስዕል ልዩ ፍቅር ነበረው። ሙዚቃ፣ እንስሳትንና እፅዋትን መንከባከብ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ ውስጥ ጊዜ ማሳለፍ ከልጅነት ፍላጎቶቹ መካከል ነበሩ። የእነዚያን ዓመታት ልምድ ሲያስታውስ፣ ለጥበብ ያለው ጉጉት ለሕያው ዓለም ከነበረው ትኩረት ጋር አብሮ ይታያል።
ይህ የልጅነት ፍላጎት ወደ ተከታታይ የጥበብ ትምህርት አደገ። በአቢሲኒያ የስነ ጥበብና የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ቀለም ቅብ ተምሮ በ2013 እ.ኤ.አ. የምስክር ወረቀት አገኘ። በ2016 እ.ኤ.አ. በእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የኪነ ጥበባት ክፍል በዲፕሎማ ተመረቀ። በ2022 እ.ኤ.አ. ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የስነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የቀለም ቅብ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ዛሬ በአዲስ አበባ የሙሉ ጊዜ ስቱዲዮ አርቲስት ሆኖ ይሠራል፤ ስቱዲዮውም ዶጭዬ አርት ስቱዲዮ ይባላል።
ሥራዎቹ ወደ ራስ ወዳድነት ጥያቄ ደጋግመው ይመለሳሉ። ብርሃኑ ይህንን ስሜት የግል ብቻ ሳይሆን፣ በቤተሰብ፣ በሃይማኖት፣ በባህል እና በማኅበራዊ ልምድ የሚቀረጽ እንደሆነ ይመለከታል። ለሌሎች ቦታ የማይሰጥ ፍላጎት እያደገ ሲሄድ በግንኙነቶች፣ በማኅበረሰቦች እና በተፈጥሮ ላይ የሚፈጥረው ጫና የሥራው ዋና ትኩረት ነው።
ብርሃኑ በጥበብ ጉዞው በርካታ ሽልማቶችን አግኝቷል፤ በአዲስ አበባ በግልና በቡድን ኤግዚቢሽኖችም ሥራዎቹን አቅርቧል። በፈንዲቃ ጋለሪ እና በጣሊያን የባህል ተቋም ከተካሄዱ የግል ኤግዚቢሽኖቹ በተጨማሪ፣ በከተማዋ ባሉ ጋለሪዎች፣ የባህል ተቋማት እና ሌሎች ቦታዎች በቡድን ኤግዚቢሽኖች ተሳትፏል።
